የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የእርስ በእርስ ትስስር በማጠናከር ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።
የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በሀገሪቱ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲያድግ፣ ምርትና አገልግሎቶች እንዲታወቁ ሚናቸው ከፍተኛ ነው። የአዲስ አበባ የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይቱ የተገኙት በአዲስ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጳውሎስ ኩሳ ሀገር የሚያድገው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ሲያድግ እንደሆነ ገልጸው መንግስት ባለፉት የለውጥ አመታት ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
አምራቾች በስራ እድል ፈጠራ፣ ገቢ ምርት በመተካት፣የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት ለከተማችን ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የገለጹት አቶ ጳውሎስ የአዲስ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ለአምራች ኢንዱስትሪው የመሳሪያ እና ማስፋፊያ ቦታ አቅርቦት፣የፋይናንስ እና ሊዝ ማሽን ብድር እና ሌሎች ቴክኒካል ድጋፎች በማመቻቸት የዘርፉን ምርታማነት ማሳደግ እንደተቻለ ገልጸዋል።
በቀጣይም ም/ቤቱን ለማጠናከር የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ ጳውሎስ ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ኢንጂነር አበበ ጉርሜሳ በበኩላቸው የአዲስ አበባ የዘርፍ ማህበራት ም/ቤት በዋናነት አምራቾችን በመደገፍ ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንደሆነ ገልጸው አምራቾች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ በተደራጀ መልኩ ይበልጥ መስራትና መደገፍ እንደሚገባ ኢንጂነር አበበ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ለዘርፉ ለሚያደርገው ድጋፍ አመስግነው በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሲሉ ኢ/ር አበበ አሳስበዋል፡፡
ምክር ቤቱ ከውጭ ሀገር አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር ግንኙነት መፍጠርና የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር መፈለግ፣ በንግድ ስራ ላይ ለሚፈጠር ችግር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን መፍትሄ መፈለግ ፣ የሚመለከታቸውን አካላት በማስፈቀድ በሀገር ውጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የንግድ ትርኢት ማዘጋጀትና መሳተፍ ዋና ተግባሩ እንደሆነም ተገልጿል።
ምክር ቤቱ በቀጣይ "የአዲስ ምርት" በሚል መሪ ቃል ደማቅ ባዛርና ኤግዚቢሽን ለማካሄድ ዝግጅት ማጠናቀቁም በፕሮግራሙ ተመላክቷል።
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments