የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እና ገበያን ለማረጋጋት ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኑሮ ውድነት ለመቀነስ እና ገበያን ለማረጋጋት ቀደም ብሎ የጀመራቸውን የገበያ ማረጋጋት ሥራዎች አጠናክሮ መቀጠሉን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ጃንጥራር አባይ አስታወቁ።
ምክትል ከንቲባው በዛሬው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት፤ አስተዳደሩ በተለይ ከነዳጅ አቅርቦት እጥረት ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን የዋጋ ንረትና የገበያ አለመረጋጋት ለመግታት ሰፋ ያሉ ሥራዎችን እያከናዎኑ ይገኛል።
የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የፍጆታ ምርቶች እጥረት እንዳይከሰት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናዎናቸውን የገለጹት አቶ ጃንጥራር፤ ለበዓሉ ፍጆታ የሚውሉ እንደ እንስሳት፣ ተዋጽኦ፣ የሰብል ምርቶች፣የግብርና እና ኢንዱስትሪ ምርቶች መሰል መሠረታዊ ግብዓቶች ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ወደ ከተማዋ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል።
ምርቶቹን ወደ ከተማችን ለሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች የነዳጅ እጥረት እንዳያጋጥማቸውና የንግድ ሰንሰለቱ እንዳይስተጓጎል በነዳጅ አቅርቦት ቅድሚያ በመስጠት ምርት እንዲገባ እየተደረገ እንደሆነም ምክትል ከንቲባው ጠቁመዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ገበያ በማረጋጋት ሥራ ዋነኛ ትኩረት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ መሆኑን የገለጹት አቶ ጃንጥራር ዜጎች የሚፈልጓቸውን መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች በቅርበት በሚገኙ ሸማቾች ማኅበራት፣በገበያ ማዕከላት እና በባዛሮች በኩል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ጠቁመዋል።
በመጨረሻም፣ የከተማ አስተዳደሩ ከነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ የገበያ መዛባቶችን በመከታተልና የአቅርቦት ሰንሰለቱን በማጠናከር፣ ምርት በስፋት ለማቅረብ የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አቶ ጃንጥራር አባይ ገልጸዋል።
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments