የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ተከናወነ።
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ በሚገኘው የምገባ ማዕከል የዘንድሮውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ ለተመጋቢዎችና ለተቸገሩ ወገኖች ልዩ የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ተከናውኗል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ጃንጥራር አባይ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በከተማዋ ከ28 በላይ የምገባ ማዕከላት ተገንብተው በቀን አንድ ጊዜ መመገብ ለማይችሉ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞችና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ተግባር መንግስት ለዜጎቹ ካለው ሰብአዊ ኃላፊነት ባሻገር እንደ አቶ በላይነህ ክንዴ ያሉ ባለሀብቶች በከፍተኛ ልግስና እያደረጉት ያለው ድጋፍ ውጤት መሆኑን አውስተው ማዕድ የማጋራት መርሃ ግብሩን በይፋ አስጀምረዋል።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ምስክር ነጋሽ (ዶ/ር) በመልዕክታቸው በበዓላት ወቅት መደጋገፍና ማካፈል የኢትዮጵያውያን የቆየ እሴት መሆኑን በመጥቀስ፣ ለዚህ በጎ ተግባር ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉት ለከንቲባ ጽ/ቤት፣ ለምገባ ኤጀንሲ እንዲሁም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ አገልግሎት ለሚሰጡ የማዕከሉ ሠራተኞች ምስጋና አቅርበዋል።
የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ባለቤት የሆኑት እና የBKG መስራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ በላይነህ ክንዴ በበኩላቸው፣ ድርጅታቸው ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ካለ ማካፈልን እንደ ትልቅ ዕድል እንደሚመለከቱት የገለጹት ባለሀብቱ፣ በየዓመቱ በዓላት ሲመጡ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር ለዜጎች ማዕድ የማጋራት ተግባርን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments