የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአምራቾችን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት እያሳደገ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በቅርቡ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ተመርቆ ወደ ስራ የገባው የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የአምራቾችን ምርታማነት በማሳደግና ተወዳዳሪነታቸውን በመጨመር ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ በፓርኩ ውስጥ የሚሰሩ አምራቾች ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ የሆነውን የኢንዱስትሪ መንደር በማስፋፋት፣ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ በትኩረት እየሰራ ይገኛል። ሰሞኑን ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ይህ ዘመናዊ የኢንዱስትሪ ፓርክም የከተማዋን የኢኮኖሚ አቅም ከመገንባት ባለፈ፣ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ ተስፋ ጥሏል።
በዚህ ዘመናዊ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ተጠቃሚ መሆን ከቻሉት አምራቾች መካከል የ“ዘመኑ ታከለና ጓደኞቻቸው ሽርክና ማህበር” መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ዘመኑ መለሰ አንዱ ናቸው።
አቶ ዘመኑ ማህበራቸው በ2010 ዓ.ም በ60 ካሬ ሜትር ጠባብ ቦታ ላይ በትንሽ አቅም የፈሳሽ ሳሙና ማምረት ስራ እንደጀመረ ያስታውሳሉ
ዛሬ ላይ ግን ከከተማ አስተዳደሩ በተደረገላቸው ድጋፍና ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ በመግባታቸው አቅማቸውን በማሳደግ፣ ከ106 በላይ ለሆኑ ዜጎች የተረጋጋ የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉ ትልቅ አምራች መሆን ችለዋል።
በፓርኩ ውስጥ በአንድ የኢንዱስትሪ መንደር መደራጀታቸው በመካከላቸው ጠንካራ የእርስ በእርስ የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ፣ በአምራቾችና በሸማቾች መካከል የላቀ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር መንገድ መክፈቱን አቶ ዘመኑ ጠቁመዋል፡፡
"ይህ ኢንዱስትሪ ፓርክ አስፈላጊው መሰረተ ልማት የተሟላለት በመሆኑ ምርታማነታችንን ለማሳደግና በገበያው ላይ ይበልጥ ተወዳዳሪ እንድንሆን ትልቅ አቅም ሆኖናል" ሲሉ አቶ ዘመኑ ገልጸዋል።
በቀጣይም የማምረት አቅማቸውን ይበልጥ በማሳደግ፣ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለሀገር ውስጥ ገበያ በስፋት ለማቅረብ አቅደዋል። በዚህም ሰፊ የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ፣ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በመሸፈን የውጭ ምንዛሬን ለማዳን በቁርጠኝነትና በትኩረት እንደሚሰሩ አቶ ዘመኑ አስታውቀዋል።
የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ መከፈት የከተማዋን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግርና የ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄን ግብ የሚያሳካ ትልቅ የልማት ምዕራፍ ነው።
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments