በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የተገነቡ የህዝብ መገልገያ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የተገነቡ የተለያዩ የህዝብ መገልገያ ፕሮጀክቶች የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ጃንጥራር አባይ በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት ለአገልግሎት ክፍት ማድረጉ ይታወሳል።
በዛሬው ዕለትም ይህንን የልማት ጉዞ የሚያጠናክሩ የህዝብ መገልገያ ፕሮጀክቶች በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ተጠናቀው ተመርቀዋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ከንቲባው እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ጃንጥራር አባይ፣ የከተማ አስተዳደሩ ትላልቅ የገበያ ማዕከላትና የኢንዱስትሪ መንደሮችን በመገንባት ለህዝብ አገልግሎት ማብቃቱን አስታውሰዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይም ዘላቂነት ያላቸውንና “ሰው ተኮር” የሆኑ የልማት ግንባታዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
አቶ ጃንጥራር አክለውም፦ "እንዲህ አይነት የልማት ስራዎችን በየቦታው ማስፋት ከቻልን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንችላለን" በማለት፣ በተለይም የኑሮ ውድነትን ለመከላከል ገበያን ማስፋት እንዲሁም የሚሰሩ እና የሚያመርቱ እጆችን ማብዛትና መደገፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በዋናነት በሁሉም ዘርፍ የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች በጥራት አጠናቆ ለህብረተሰቡ ማስረከብ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በትምህርትና ዘርፍ በርካታ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች የተገነቡ ሲሆን፣ በጤናው ዘርፍ ደግሞ ደረጃቸውን የጠበቁ ትላልቅ ሆስፒታሎችን የመገንባትና የማደስ ስራዎች እንደተሰሩ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በቤት ልማት ፕሮግራም፣ በኢንዱስትሪ መንደር ግንባታ እና በሌሎችም የልማት ዘርፎች በርካታ ውጤታማ ስራዎች ተመዝግበዋል።
ይህ ስኬት ሊመዘገብ የቻለው አመራሩ ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት በየቀኑ በ24 ሰዓት (7/24) ቀጣይነት ባለው ትጋት መስራት በመቻሉ መሆኑን አቶ ጃንጥራር ገልጸው፣ በቀጣይም በርካታ የልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም አመራሩ በቀጣይነት የህዝብ ጥያቄ የሆኑ መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ይበልጥ በትኩረት መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል።
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments