አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍና ምርታማነታቸውን በማሳደግ ረገድ ውጤታማ ስራዎች እንደተሰሩ ክቡር አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ፡፡
ባለፉት አስር ወራት አምራች ኢንዱስትሪዎችን በቁርጠኝነት በመደገፍና ምርታማነታቸውን በማሳደግ ረገድ አበረታችና ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ፡፡
ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ፤ የቢሮው ማዕከል አመራሮች፣ ዳይሬክተሮች እና የክፍለ ከተማ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች በተገኙበት ባለፉት አስር ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ በበየነ መረብ (Zoom) የግምገማ መድረክ አካሂደዋል፡፡
ክቡር አቶ ጃንጥራር አባይ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች፦ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት፣ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት፣ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር፣ እንዲሁም አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቱን በማፋጠን ረገድ ግንባር ቀደም እና ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አምራቾች ከፍተኛ ምርት በስፋትና በጥራት በማምረት የገበያ እጥረትን በመቅረፍ፣ የኑሮ ውድነትን በመቀነስ እና ገበያን በማረጋጋት ረገድ ያላቸው ሚና እጅግ የጎላ መሆኑን ምክትል ከንቲባው አስገንዝበዋል።
በመሆኑም በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ባለሙያ በየክፍለ ከተማው ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በአግባቡ በመለየት፣ ዘርፉ የሚፈልገውን ተገቢውን ድጋፍና ቀጣይነት ያለው ክትትል አጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በመጨረሻም፣ በበጀት ዓመቱ ታቅደው የተከናወኑ ስኬቶችን ይበልጥ በማስቀጠል፣ በተለያዩ ምክንያቶች ያልተከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር በመለየት በቀሪዎቹ ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ በትኩረትና በላቀ ተነሳሽነት መስራት እንደሚገባ ክቡር አቶ ጃንጥራር አባይ አሳስበዋል።
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments