ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት የኢኮኖሚ ብልፅግና ዋስትና ነው፤ ማነቆዎችን በመፍታት አምራቾችን እየደገፍን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ ፡፤
የኢኮኖሚ ብልፅግናን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚቻለው አምራች ኢንዱስትሪዎች ሲስፋፉና ሲያድጉ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።
ምክትል ከንቲባው ይህንን ያሉት የከተማ አስተዳደሩ፣ የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ እና የመስሪያ ቦታዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ በጋራ ባዘጋጁት የማምረቻ ቦታ የማስተላለፍ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው።
አቶ ጃንጥራር በንግግራቸው፤ የዓለማችን ታላላቅና ኃያላን ሀገራት የበለጸጉት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠታቸውና ዘመናዊ የኢንዱስትሪ መንደሮችን በመገንባታቸው መሆኑን በታሪክ የተረጋገጠ እውነታ ነው ብለዋል።
መንግስት ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንደሆነ የጠቀሱት ምክትል ከንቲባው፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ራሱን ችሎ የተገነባውና ለተጠቃሚዎች እየተላለፈ ያለው ፓርክ የዚህ ትኩረት ማሳያዎች መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
እውነተኛ ኢንደስትራላይዜሽን ሊረጋገጥ የሚችለው አምራቾች የሥራ ባህላቸውን ሲያሻሽሉ፣ የምርት ጥራትና ተወዳዳሪነትን ሲያረጋግጡ፣ ስትራቴጂካዊ የሆኑ ገቢ ምርቶችን በመተካት ረገድ የበኩላቸውን ሲወጡ እና በመካከላቸው ውጤታማ ትስስር ሲፈጥሩ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዛሬው እለትም በ2018 ዓ.ም የአዲስ እና የማስፋፊያ የማምረቻ ቦታ ጥያቄ አቅርበው በየደረጃው በነበረው አደረጃጀት የጸደቀላቸው 28 አዲስ ተከራይተው ይሰሩ የነበሩ እና 24 የማስፋፊያ ጥያቄ ያቀረቡ ነባር አምራች ኢንዱስትሪዎች (በአጠቃላይ 52 አምራቾች) የማምረቻ ቦታ ርክክብ ተደርጎላቸዋል።
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments