ኢትዮጵያ ታምርት፣ አዲስ አበባ ትበልጽግ!” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ኮንቬንሽን ማዕከል በድምቀት ተጀመረ።
በመክፈቻው ሥነ-ስርዓት የአዲስ አበባ ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ምኒስትር ክቡር አቶ መላኩ አለበል ፣ ምክትል ከንቲባ የተከበሩ አቶ ጃንጥራር አባይን ጨምሮ የፌደራል እና የከተማ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና አምራቾች ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ጃንጥራር አባይ በንግግራቸው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የመንግስት ዋና የልማት ትኩረት መሆኑን ገልጸው፣ ከተማዋም ዘርፉን በልዩ ትኩረት እየደገፈች መሆኗን አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መንግስትና አምራቾች በቅርበት እንዲሰሩ የሚያስችል መድረክ መፍጠሩንም ጠቁመዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት የነበረውን የአምራች ኢንዱስትሪዎች የምርት አጠቃቀም ከ30 በመቶ ወደ 45 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጸው፣ የማምረት አቅም አጠቃቀም 69.9 በመቶ ደርሶ ወደ 85 በመቶ ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የተከበሩ አቶ ጃንጥራር ተናግረዋል።
በከተማዋ ከ3,890 በላይ አምራቾች እንዳሉ እና ከእነዚህ ውስጥ ከ2,000 በላይ ተኪ ምርት እንደሚያመርቱ ገልጸዋል። ወደ ውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አምራቾችም 200 መድረሳቸውን አስታውቀዋል።
የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የዘርፉን ችግሮች በመለየት ከባንኮች፣ ከሊዝ አቅራቢዎች፣ ከመሰረተ ልማት ተቋማት፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑ ተገልጿል። በቀጣይም ሮድ ማፕ፣ የተፅዕኖ ግምገማና የተለያዩ ስትራቴጂዎች ለመቅረጽ ጥናቶች እየተካሄዱ ነው።
አቶ ጃንጥራር አክለውም ዘርፉ የሚፈልገው ለውጥ በአንድ ተቋም ብቻ እንደማይሳካ በመግለጽ፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ኃላፊነታቸውን በትጋት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በመጨረሻም መርሃ ግብሩ እንዲሳካ ድጋፍ ላደረጉ አመራሮችና ሰራተኞችም አቶ ጃንጥራር አባይ ምስጋና አቅርበዋል።
#ኢትዮጵያ_ታምርት_አዲስ_አበባ_ትበልጽግ!
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments